"በሴቶች ተሳትፎ የፀናችና የበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በአርባምንጭ ከተማ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው
የካቲት 9/2018 ዓ.ም
"በሴቶች ተሳትፎ የፀናችና የበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የስልጤ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የፌደራል ሴቶች ክንፍ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ነኢማ ሙኒር እንደገለጹት ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ መስክ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ኢትዮጵያን ተምሳሌት ሀገር ለማድረግ የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ነኢማ፤ ሴቶች በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደቡብ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ምህረት በላይ በበኩላቸው የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፓርቲው በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የጋሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ የመደመር መንግስት አንዱና ዋነኛው ዓላማ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ሀገር ግንባታ ሂደት ሴቶች ሚናቸውን በትኩረት እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በተለይም የኑሮ ውድነትን ከመከላከል አኳያ በከተማ ግብርና ላይ የታየው የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአርባምንጭ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ከንቲባ በበኩላቸውበለውጡ መንግስት ሴቶች በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎች በመሰራታቸው አስደናቂ ለውጥ መታየቱን ገልጸው፤ ሴቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ "በሴቶች ተሳትፎ የፀናችና የበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ የውይይት ሰነድ ቀርቦ ምክክር እየተደረገበት ይገኛል።
በዚህ የንቅናቄ መድረክ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የከተማው ሴት አመራሮች፣ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።