በየደረጃው ያለው የፓርቲ መዋቅር ከምርጫ ማግስት ወደ መደበኛ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል :- ክብርት ወ/ሮ ነኢማ ሙኒር
ሰኔ 15/2018 የስልጤ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት
በየ ደረጃዉ ያለዉ የፓርቲ መዋቅር ከምርጫ ማግስት ወደ መደበኛ የፓርቲ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የህዝቡን የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመመለስ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት የስልጤ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ነኢማ ሙኒር ገለፁ።
ኃላፊዋ ይህንን ያሉት የዞኑ የፓርቲ ኮሚቴ በ15ቱም መዋቅሮች ላይ ሲያካሂድ የቆየውን የፓርቲ መደበኛ እና የድህረ ምርጫ ስራዎች ያለበትን ደረጃ የድጋፍና ክትትል ስራ ባጠናቀቀበት ወቅት ሲሆን፣ በወቅቱም የፓርቲው የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሁሴን ሱነሞ እና የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሳሊያ ሀሰንን ጨምሮ የፓርቲው አመራሮች ተገኝተዋል።
በሂደቱም ከምርጫው ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ የነበሩ የተቀናጁ የመረጃ ቅብብሎሾች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የገለጹት ወ/ሮ ነኢማ ሙኒር የምርጫ ኮሚቴው፣ የልማት ኮሚቴው፣ የመልካም አስተዳደርና የፀጥታ ኮሚቴዎች በቅንጅት የሰሯቸውን ስራዎች ቀጣይ በሚኖሩ የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ልማት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ መድገም ያስፈልጋል ብለዋል።
ከምርጫ ማግስት የተካሄደው የድጋፍና ክትትል ስራ ዝም ብሎ የተለመደ ግምገማ ሳይሆን፣ በምርጫው ሂደት የታዩ ጠንካራ ጎኖችን ወደ መደበኛ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች የምናሸጋግርበት ወቅት በመሆኑ አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ አደረጃጀቶችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይጠበቅበታል ሲሉም አፅኖት ሰተው ገልፀዋል።
ክብርት ወ/ሮ ነኢማ አክለውም በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዞኑ ህዝብ የሰጠውን የሀገር አደራ በሚገባ ለመወጣት አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበትና በምርጫ ወቅት ያሳየውን ርብርብ በድህረ ምርጫ ወቅትም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሂደቱ የታየው የተቀናጀ የመረጃ ቅብብልና የአመራሩ ቁርጠኝነት በቀጣይ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን በመቅረፍ የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ጥያቄዎችን በፍጥነት ለመመለስ ሊያገለግል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ምርጫው ዜጎችን በነፃነት እና በሰላማዊ መንገድ ፍላጎታቸውን ያንጸባረቁበት ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያ ወደፊት ለምትጓዝበት የብልፅግና መስመር አስተማማኝ መሰረት የጣለ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፣ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ግልጽና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተደረጉ የተቀናጁ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በመሆኑም በምርጫው የተገኘው የህዝብ አመኔታ ወደ ላቀ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራ መተርጎም ያስፈልጋል ያሉት ክብርት ወ/ሮ ነኢማ በዞኑ የተጀመሩ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፍ ስራዎችን በቁርጠኝነት በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ በቅንጅት መስራት ይኖርበታል ብለዋል።
ልማትን በማፋጠን እና ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት የህዝቡን የብልፅግና ተስፋ ወደ ማይቀለበስ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ የጠቆሙት ወ/ሮ ነኢማ አመራሩ በሙሉ አቅሙ ወደ መደበኛ ስራው መመለስና በድህረ-ምርጫ ወቅት ለሚከናወኑ ተግባራት ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።
ተቻችለንና ተደማምጠን በምርጫው መንትያ ግቦችን አሳክተናል ያሉት ክብርት ነኢማ ይህንን ስኬት በልማት መድገም እንደሚገባና ከመላው ህዝባችን ጋር በመሆን የተጀመሩና አዳዲስ የልማት ስራዎችን ለመረጠን ህዝብ በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በቁርጠኝነት መፍታት፣ የዞኑን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ እና ሌሎች በልዩ ዕቅድ የታቀዱ ተግባራትን መፈጸም እንደሚገባ የገለጹት ወ/ሮ ነኢማ፣ የድህረ ምርጫው ምዕራፍ ከመድከም እና በውጤት ከመርካት ይልቅ ቃልን በተግባር የምናሳይበትና የህዝብን አመኔታ ይበልጥ የምናጠናክርበት ወቅት ነው ብለዋል።
ከድህረ ምርጫ በኋላ ብቁና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዕቅድ በማዘጋጀት ስራዎችን መስራት እንደሚገባና ፓርቲው በዛሬው ውጤት ረክቶ የሚቆም ሳይሆን ለትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ስራዎችን በመስራት የኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ቃልን በተግባር ማዋል፣ የህዝብ ጥያቄዎችን በመልካም አስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ በብቃት መመለስ እና የመደመር እሳቤን ማጠናከር ቀጣይ ተግባራችን ነው ያሉት ክብርት ወ/ሮ ነኢማ ሙኒር በምርጫው ሂደት የታዩ የአደረጃጀትና የንቅናቄ ክፍተቶችን በግልጽ በመገምገም እና በመሙላት ከህዝብ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የህዝቡ የልማት ጥያቄዎች የወደፊት ዕቅዶች ዋነኛ አካል መሆን እንዳለባቸው በመግለፅ በምርጫው ወቅት የተመዘገበው ስኬታማ አንድነት በቀጥታ ወደ ልማትና ምርታማነት ተግባራት መዞር እንዳለበትና በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት የመንግስትና የፓርቲ መደበኛ ስራዎች ሳይንጠባጠቡ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በአፅንኦት አሳስበዋል።

































