የወራቤ የሀይል ማከፋፈያ ጣቢያ መንግስት የህዝብ ፍላጎቶችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ያለውን የላቀ ቁርጠኝነት ያረጋገጠበት መሆኑ ተገለጸ።

የወራቤ የሀይል ማከፋፈያ ጣቢያ መንግስት የህዝብ ፍላጎቶችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ያለውን የላቀ ቁርጠኝነት ያረጋገጠበት መሆኑ ተገለጸ።

 

ግንቦት 14/2018 ዓ.ም በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በ 640 ሚሊየን ብር የተገነባው የወራቤ ዘመናዊ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የኢፌዴሪ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ጊስቲት ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ  አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
 
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ጊስቲት ሙፈሪያት ካሚል ፕሮጀክቱ የለውጡ መንግስት የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት ከወሰደው ቁርጠኝነት መነሻ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

የለውጡ መንግስት ከኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ባሻገር በሌሎች የህዝብን ችግር በሚፈቱና ኑሮውን በሚያሻሽሉ ዘርፎች መጠነ ሰፊ ውጤት ማስመዝገቡን ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በዞኑ አመራር በኩል አደራን የመቀባበልና የልማት ስራዎችን የማስቀጠል ልምዶች እንዲሁም የህዝቡ የልማት ተባባሪነት ለፕሮጀክቱ መሳካት ከፍ ያለ ሚና እንደነበረው የጠቆሙት ክብርት ሙፈሪያት ይህ በጎ ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ ባለፉት ዓመታት የሀይል እጥረትና መቆራረጥ የዞኑ ዋነኛ ችግር ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከሀይል እጥረትና መቆራረጥ መነሻ ብዙ ባለሃብቶች ለኪሳራ ከመዳረግ ባሻገር በርካቶች የኢንቨስተመንት ስራቸውን አቋርጠው መሄዳቸውን አቶ ዘይኔ አስታውሰዋል።

በለውጡ መንግስት በተወሰደ ቁርጠኝነት የወራቤ የሀይል ማከፋፈያ ጣቢያ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው የጣቢያው መገንባት የዞኑን ህዝብ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች መመለሱን አስረድተዋል።

በጣቢያው ግንባታ ወራቤን ጨምሮ በርካታ አከባቢዎች የተሟላ የመብራት አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውንና በልዩነትም የኢንዱስትሪ ዘርፉን በሰፊው እያገዘ መሆኑን አቶ ዘይኔ ተናግረዋል።

አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) በበኩላቸው  የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ወደ ሥራ መግባቱ በወራቤ ከተማና ዙሪያ አስተማማኝና ጥራቱን የጠበቀ የኃይል አቅርቦት ለመዘርጋት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ጣቢያው ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የቮልቴጅ መውረድና መቆራረጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚያቃልል መሆኑንም ኢንጂነሩ ገልጸዋል፡፡

gallery try zoom