በወራቤ ከተማ ከ1.25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የልማት ፕሮጀክቶች በይፋ ተመረቁ፦

በወራቤ ከተማ ከ1.25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የልማት ፕሮጀክቶች በይፋ ተመረቁ፦

 

ወራቤ ግንቦት 14/2018ወራቤ ከተማ አስተዳደር ከ1.25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን በይፋ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ጊስት ሙፈሪያት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት ሀገሪቱ በአስቸጋሪ የውስጥና የውጭ ጫናዎች ውስጥ ብትሆንም በርካታ የልማትና የዲሞክራሲ ድሎችን ማስመዝገብ መቻሏን ገልፀዋል።

ያለፉት የለውጥ አመታት የፖለቲካና የተቋም ግንባታ የተሰራባቸው ትልልቅ ስኬቶች የተመዘገቡባቸው ዓመታት ናቸውም ብለዋል

በወራቤ ከተማ የተከናወኑ ፕሮጀክቶች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የወንዝ ዳርቻና ፓርኩ ግንባታ ለከተማዋ ህብረተሰብ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

ፓርኩ የስልጤን ባህላዊ ቤቶችና የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ውበት ከፍ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑንም አብራርተዋል።

ከዚህ በፊት ያልነበሩ ብዙ ነገሮች ዛሬ እውን ሆነዋል ያሉት ጊስት ሙፈሪያት በመንግስትና በህዝብ የጋራ ጥረት ወራቤን የኢንዱስትሪ መንደር ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በማህበራዊ ዘርፍም በከተማ አስተዳደሩ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ ልማቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በመንገድ መሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።

ከህዝብ ፍላጎት የሚነሱ የልማት ስራዎች በሁሉም ዘርፍ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

የስልጤ ህዝብ ሰላም ወዳድ ነው “ሰላም ለስልጤ ህዝብ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ነው” ብለዋል።

የወራቤ መጪ ዘመን ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከተማዋ ለልማት ምቹ መሆኗና የህዝቡ ታታሪነት ከተጨመረበት ወራቤ በቀጣይ ትልቅ እድገት እንደምታሳይ ገልፀዋል።

የካሊድ ድጆ የመስኖ ፕሮጀክት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲስ ስራዎችን በመጀመር የወራቤ ልማት የበለጠ እንደሚያድግ ተናግረዋል።

በተለይም ወጣቶች በክህሎት ከታጠቁ የወደፊቱ ትውልድ የተሻለ እድል እንደሚያገኝ ገልፀው፤በአካባቢው የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

gallery try zoom