የስልጤ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ህንጻ
የስልጤ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ህንጻ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዝሃነት ውብ ተምሳሌት ናት። የተለያዩ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና የፖለቲካ አመለካከቶች በአንድነት የደመቁባት ታላቅ ምድር ናት ዜጎቿ በልዩነቶቻቸው ሳይከፋፈሉ፣ ልዩነታቸውን የውበታቸውና የጥንካሬያቸው መገለጫ አድርገው፣ በመከባበርና በመቻቻል ለዘመናት አብረው ኖረዋል። ውድ ህይወታቸውን በመሥዋዕትነት በመክፈልም የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና ነፃነት አስከብረው ለእኛ አስረክበውናል።
ነገር ግን ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የተፈጠሩ የተዛቡ ትረካዎችና የፖለቲካ አመለካከቶች ይህንን የጋራ እውነታችንን ለመሸርሸር ሞክረዋል። አባቶቻችን የሀገር ምሰሶ ያደረጓቸውን እሴቶች የጥንካሬ ሳይሆን የድክመት ምንጭ ለማድረግ የሰሩ ኃይሎች ጥቂት አይደሉም። አልፎ ተርፎም፣ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች በችግሮች ላይ ቤንዚን በመጨመር መከራችንን ሲያራዝሙት፣ ሌሎቹ ደግሞ ግልጽ ያልሆኑ መፍትሔዎችን በመስጠት ችግሩን ይበልጥ ሲያወሳስቡት ቆይተዋል። የሀገራዊ ለውጡ ፈናጣቂ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ ግን የሀገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች በዘላቂነት መፈወስ የሚቻለው በአገራዊ አንድነትና በወንድማማችነት/እህትማማችነት ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ እንደሆነ በፅኑ ያምናል። ለዚህም ነው አገራዊ አንድነታችንን በሕግ፣ በአሠራርና በተቋም ደረጃ የትኩረታችን ማዕከል ያደረግነው።
በዚህ ታላቅ ጉዞ ውስጥ የስልጤ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በዞኑ ነዋሪዎች የተጣለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል። ባለፉት አምስት ዓመታት የሰላም ሰገነት በሆነችው በስልጤ ዞን የኢትዮጵያ ብልፅግና የማይቀለበስ መሆኑን ያረጋገጡ አበይት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ድሎችን አስመዝግበናል በወራቤ ከተማችንም ደማቅ የብልጽግና አሻራ አኑረናል። እርግጥ ነው በጉዟችን ላይ ፈተናዎች አጋጥመውናል። ሆኖም እኛ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ፣ አቅማችንን ወደ ላቀ ውጤት፣ ተግዳሮቶችንም ወደ ታላቅ ስኬት በመቀየር በመተሳሰብና በወንድማማችነት እጅ ለእጅ ተያይዘን ታላቋን ኢትዮጵያን ብሎም ውዱን የስልጤን ሕዝብ ከፍ ለማድረግ በፅናት ወደፊት ተጉዘናል ጉዟችንንም እንቀጥላለን!" በዞናችን በየደረጃው የምትገኙ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መላው ማህበረሰብ የውስጥ አንድነታችንን ይበልጥ በማጠናከር ድህነትን፣ ስንፍናን፣ ሌብነትንና ሙስናን በቆራጥነት በመታገል የድካማችን ማማ፣ የልፋታችን ውጤት የሆነውን ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን ማረጋገጥ የምንችለው በዚህ ትግል ነው። በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ የዞናችን ነዋሪዎች እንደ ሁልጊዜው የጽናት አለኝታችንና የጉዟችን ደጋፊዎች ሆናችሁ ከጎናችን እንደምትቆሙ ሙሉ እምነት አለን። በመጨረሻም፣ ለዴሞክራሲያችን መጎልበት የማይተካ ሚና ያላችሁ ተፎካካሪ የፖሎቲካ ፓርቲዎች ለታላቋ ኢትዮጵያና ለክቡር ሕዝቧ ብልፅግና ሲባል በትብብርና በጋራ እንድንቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ። ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት፣ ፍቅርና ልፋት ትበለጽጋለች!
አመሰግናለሁ!"